Showing posts with label የቅዱሳን_ሕይወት. Show all posts
Showing posts with label የቅዱሳን_ሕይወት. Show all posts

Wednesday, March 25, 2015

አብርሃ ወአጽብሐ

ቅዱሳን ነገስታት አብርሃ ወአጽብሐ አባታቸው ታዜር እናታቸው ሶፍያ/አህየዋ/ በቅድስና የሚኖሩ እግዚአብሔርን በቅድስና በንጽህና የሚያገለግሉ ነገር ግን ልጅ ያላገኙ መካኖች ነበሩ። ስለሆነም ጌታ ሆይ ደስ የሚያሰኝህ በትዕዛዝህም የሚኖር ልጅ ስጠን እያሉ እግዚአብሔርን ይለምኑ ነበር፡፡

ከዕለታት አንድ ቀን ስለ እግዚአብሔር ቸርነት ሲነጋገሩ ንግስት ሶፍያ የሐና እመ ሳሙኤልን ጸሎት በመጥቀስ እሷም እንደ ሐና ሱባኤ ገብታ ፈጣሪዋን እንድትለምን ንጉሱን ጠየቀችው፡ ንጉሱም “ ኦ ብእሲቶ ሰናየ ኁለይኪ” አንቺ ሆይ መልካም አስበሻል በማለት በምክሯ ተስማምቶ ሱባኤ ገብታ ፈጣሪዋን በጸሎት እንድትጠይቅ ፈቀደላት፡፡ ንግስት ሶፍያም የካቲት 18 ቀን ሱባኤ ገብታ ፈጣሪዋን መለመን ጀመረች፡፡ ከጸሎቷም ጥቂቱ “ በኪሩቤል ላይ የምትኖር፣ የቀለያትንም (ጥልቅ ባህርንም) የምትመለከት ጌታዬ ፈጠሪዬ ሆይ አቤቱ ጸሎቴንና ልመንያን ስማኝ፣ ልቅሶየንም አድምጥ ቸላ አትበለኝ” የሚል ነበር፡፡

ደጓ ንግስት ሶፍያ በብዙ ጸሎትና እንባ ሱባኤዋን ለመጨረስ ስትቃረብ፣ አንድ ራእይ ተገለጠላት፣ እሱም ከተራራ ላይ የተተከለች ረዥም ዛፍ አየች፡፡ ፍሬዋም ጫፍ እስከ ጫፍ የሞላ ነበር፡፡ ጫፎቿም ምድርን የሚሸፍኑ ነበሩ፡፡ አንድ ሰው፣ ብርሃን ለብሶ ብርሃን ተጎናጽፎ፣ በእጁም ትምህርተ መስቀል ያላት የወርቅ ዘንግ ይዞ መጣ፡፡ ሁለት መሰላልም ይዞ መሰላሎቹን ከዛች ዛፍ ግራና ቀኝ አቆማቸው፡፡ ንግስት ሶፍያ ግን የዚህ ራእይ ምስጢር አልረዳ ቢላት ተጨነቀች፣ ምስጢሩን ይገልጽላት ዘንድም

Friday, February 27, 2015

አባ ሳሙኤል ዘደብረ ሃሌ ሉያ



አባ ሳሙኤል የታላቁ ርዕሰ መነኮሳት የአባ እንጦንስ ተከታይ የደብረ ሃሌ ሉያ ገዳም መሥራች፣ በ፲፬ኛው ምዕተ ዓመት ይኖሩ የነበሩ፣ ሀብተ ትንቢት የተሰጣቸው ታላቅ አባት ናቸው፡፡ አባ ሳሙኤል የመሰረቱት ገዳም ደብረ ሃሌ ሉያ፤ በክብሩ ከደብረ ሲናና ከደብረ ዘይት የማያንስ መሆኑ ይነገርለታል፡፡ ስለ አባ ሳሙኤል ገድላቸው እንዲህ ይተርክላቸዋል፡፡
ስሟ መርታ በተባለች ሀገር የሚኖሩ፣ ሕገ እግዚአብሔርን እንደ ኖኅ እንደ አብርሃም የጠበቁ፣ በትውልድም የቡሩካን የደጋግ ሰዎች ወገን የሆኑ ስማቸው ይስሐቅ ለነ እግዚእ የሚባሉ ሰው ነበሩ፡፡ እኒህም ሰው ቅድስትነ ማርያም የምትባል ሴት በሕግ አገቡ፤ እርሷም እንደ ሃና እንደ ኤልሳቤጥ እግዚአብሔርን የምትፈራ፣ ለድሃ የምትራራና በሁሉ ዘንድ የተወደደች ነበረች፡፡ በትውልድም የክቡራን ወገን ነበረች፤ ሙት የሚያስነሱ ድውያን የሚፈውሱ አቡነ ዓቢየ እግዚእ የተባሉ ጻድቅ ወንድም ነበሯት፡፡ ልጅ እንደፀነሰችም ባወቀች ጊዜ፤ ቡራኬ ለመቀበል ወደ እርሳቸው ለመሄድ መንገድ ጀመረች፡፡ እዚያም በደረሰች ጊዜ አቡነ ዓቢየ እግዚእ ከደቀ መዛሙርቶቻቸው ጋር ሳሉ፣ እህታቸው ስትመጣ ስላዩአት፤ አጠገባቸው ከመድረሷ አስቀድሞ ግንባራቸውን መሬት አስነክተው ሰገዱላት፡፡ ደቀ መዛሙርቱም ይህን በማየታቸው በመደነቅ "አባታችን ለዚህች ሴት በምን ምክነያት ሰገዱላት?" በማለት ጠየቋቸው፡፡ እርሳቸውም "ልጆቼ ሆይ ለእርሷ የሰገድኩ አይምሰላችሁ፤ እኔ የሰገድኩት በብርሃኑ ምድረ ኢትዮጲያን ለሚያበራት፣ ዕንቁ ባሕርይ ለሆነ በማኅፀንዋ ላለው ልጅ ነው፡፡ እሱም በጸሎቱ የሚጠብቅ፣ በትሩፋቱ የሚያፀድቅ፣ በትምህርቱ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ሕዝብ የሚያድን፣ የኔንም ስም የሚያስጠራ ነው" የሚል ቃለ ትንቢት መለሱላቸው፡፡